ethiopia news

Discrepancies Emerge in Ethiopia’s Wheat Production Claims

Official claims regarding Ethiopia’s record wheat production face scrutiny as international data highlights significant statistical gaps.

ኢትዮጵያ ቼክ/- ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ሰሉልታ አካባቢ የሚገኝ የስንዴ ማሳን በጎበኙበት ወቅት ኢትዮጵያ በዘንድሮው የምርት ዘመን ያስመዘገበችውን ውጤት በተመለከተ የሰጡት መግለጫ አነጋጋሪ ሆኗል። በመግለጫቸውም ሀገሪቱ በዚህ በጀት ዓመት ከ330 ሚሊዮን ኩንታል (33 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን) በላይ ስንዴ ማምረት መቻሏንና ይህም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚዋ ስንዴ አምራች ሀገር እንደሚያደርጋት ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ይህ በመንግስት በኩል የቀረበው አሀዝ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የግብርና እና የኢኮኖሚ መረጃ ተንታኝ ተቋማት ሪፖርቶች ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ልዩነት ይታይበታል። የአሜሪካ የእርሻ ዲፓርትመንት (USDA) የውጭ እርሻ አገልግሎት (FAS) እ.ኤ.አ በኤፕሪል 2024 እና በሜይ 2025 ባወጣቸው ተከታታይ ሪፖርቶች መሰረት የኢትዮጵያ ዓመታዊ የስንዴ ምርት በ6.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን አካባቢ እንደሚገኝ ተገምቷል። ምንም እንኳን ተቋሙ በኢትዮጵያ የመስኖ ስንዴ ልማት እና የክላስተር ግብርና ምርታማነትን እየጨመረ መሆኑን ቢገልጽም የተመዘገበው ጭማሪ በመንግስት ከተጠቀሰው 33 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ጋር ሲነጻጸር በአምስት እጥፍ ገደማ ያነሰ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የሳተላይት ምስሎችን እና የመሬት ላይ መረጃዎችን መሰረት ያደረጉ የUSDA ትንታኔዎች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ ለእርሻ የዋለው መሬት ስፋት እና የተገኘው ምርት መጠን መንግስት እንደሚለው “በአራት እጥፍ” አድጓል የሚለውን መረጃ አያረጋግጡም። በተመሳሳይ እንደ FAO (የዓለም የምግብ እና ግብርና ድርጅት) ያሉ ተቋማት መረጃዎችም የኢትዮጵያን ምርት ከ7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ አያደርሱትም። ኢትዮጵያ “ግብፅን በሶስት እጥፍ በመብለጥ ከአፍሪካ አንደኛ ሆናለች” የሚለውን መግለጫ በተመለከተ ዓለም አቀፍ የንግድ እና የግብርና መረጃዎች የተለየ ምስል ያሳያሉ። የUSDA እና የኢንዴክስ ቦክስ (IndexBox) የ2024/25 ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ግብፅ በ9.2 እስከ 9.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዓመታዊ ምርት አሁንም ከአፍሪካ ቀዳሚነቱን እንደያዘች ነው። ኢትዮጵያ በ6.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ምርቷ ከግብፅ ቀጥላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። መንግስት ኢትዮጵያ ስንዴ ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች ቢልም የዓለም አቀፍ የንግድ መረጃዎች (እንደ OEC ያሉ) ግን ኢትዮጵያ አሁንም ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ ከውጭ እንደምታስገባ ያሳያሉ። ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ2024 እና 2025 መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ ከኬንያ፣ ሮማኒያ እና ቱርክ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያወጣ ስንዴ ገዝታለች። በተቃራኒው ወደ ውጭ የተላከው የምርት መጠን እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ተመዝግቧል። እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እና በዓለም ባንክ የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት፤ በሀገር ውስጥ ገበያ ላይ የታየው የስንዴ ዋጋ ንረት (በአንድ ዓመት ውስጥ የ28% ጭማሪ) እና በምግብ እርዳታ ላይ የሚገኙ ዜጎች ቁጥር አለመቀነስ፣ ሀገሪቱ “ትርፍ ምርት አምርታለች” ከሚለው መግለጫ ጋር የሚጋጩ ተጨባጭ እውነታዎች ናቸው። በአጠቃላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው የ33 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የምርት ሪፖርት ከገለልተኛ ዓለም አቀፍ ተቋማት ግምቶች (ከ5.5 – 7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን) ጋር እጅግ ሰፊ ልዩነት ያለው ሲሆን የሀገሪቱ የገቢ ንግድ መረጃ እና የገበያ ዋጋም የቀረበውን “ትርፍ ምርት” አያረጋግጡም።

Secret Link